Tuesday 3 May 2016


ሰሙነ ሕማማትሐሙስ፡-


ከስቅለትና ከትንሣኤ በፊት ያለው
ሐሙስ በቤተ ክርስቲያናችን የተለያዩ
ስያሜዎች አሉት፡፡
1.ሕጽበተ እግር ይባላል፡፡
ይህ ስያሜ የተሰጠው ጌታችን በዚህ
ዕለት የደቀ መዛሙርቱን እግር
በማጠቡ ምክንያት ነው፡፡ ይህም
የሚያሳየው የዓለምን ኃጢአት
ለማጠብ የመጣ መሆኑን ነው፡፡
ይህንን ለማስታወስ ዛሬ ካህናት
በተለይም ሊቃነ ጳጳሳት በመካከላችን
ተገኝተህ የእኛንና የሕዝቡን ኃጢአት
እጠብ ሲሉ በቤተ ክርስቲያናችን
የተገኙትን ምእመናን እግር በወይንና
በወይራ ቅጠል ሲያጥቡ ያረፍዳሉ፡፡ /
ዮሐ. 13፤4-15/
2.የጸሎት ሐሙስ ይባላል፡፡
የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ
የሚደክም ሥጋን የተዋሐደ አምላክ
ፍጹም ሰው መሆኑን ለመግለጽና
ለአርአያነት ጠላቶቹ መጥተው
እስኪይዙት ድረስ በጌቴ ሴማኒ ሲጸልይ
በማደሩ ምክንያት ነው፡፡ /ማቴ.
26፤36፣ ዮሐ. 17፤1/
3.የምስጢር ቀንም ይባላል፡፡
ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን
አንዱ በዚህ ዕለት ተመሥርቷል፡፡
ይኸውም ይህ ስለ እናንተ በመስቀል
ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው፤
እንካችሁ ብሉ፡፡ ጽዋውንም አንሥቶ
አመሰገነ ይህ ስለ እናንተ ነገ በመስቀል
የሚፈስ ደሜ ነው፤ ከእርሱም ጠጡ፡፡
በማለት እኛ ከእርሱ ጋር አንድ
የምንሆንበትን መንገድ ከጠላት
ዲያብሎስ ሰውሮ ለደቀ መዛሙርቱ
የገለጠበት ቀን በመሆኑ የተሰጠ ስያሜ
ነው፡፡
በዚህ ዕለት ቅዳሴ ይቀደሳል፡፡
የሚቀደሰውም በለሆሳስ ሲሆን እንደ
ቃጭል በመሆን የሚያገለግለውም
ጽናጽል ነው፡፡ ይህም አይሁድ ጌታችንን
ለመያዝ ሲመጡ ድምፃቸውን ዝግ
አድርገው በለሆሳስ እየተነጋገሩ
መምጣታቸውን ለማሰብ ነው፡፡
በቅዳሴውም ኑዛዜ አይደረግም፡፡
ሥርዓተ ቁርባን ግን ይፈጸምበታል፡፡
ይህም ጌታችን የሰጠውን ዘለዓለማዊ
ቃል ኪዳን ለማሰብ ነው፡፡ በዚህ ዕለት
ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በንስሐ ታጥቦ
ተዘጋጅቶ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር
ደሙን መቀበል ይኖርበታል፡፡
4.የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል፡፡
ምክንያቱም መሥዋዕተ ኦሪት
ማለትም በእንስሳ ደም የሚቀርበው
መሥዋዕት ማብቃቱን ገልጦ፣ ለድኅነተ
ዓለም ራሱን የተወደደ መሥዋዕት
አድርጎ ያቀረበበት ዕለት በመሆኑ
ነው፡፡ /ሉቃ. 22፤18-20/ ይህ ጽዋ
ስለ እናንተ በሚፈሰው ደሜ የሚሆን
የአዲስ ኪዳን ነው፡፡ ከእርሱም ጠጡ
በማለቱ ይታወቃል፡፡ ጌታችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ዘለዓማዊ ቃል
ኪዳን በራሱ ደም የፈጸመበት ዕለት
መሆኑን በማሰብ የቃል ኪዳኑ
ፈጻሚዎች ጠባቂዎች መሆን
እንደሚገባን እንማራለን፡፡
5.የነጻነት ሐሙስ ይባላል፡፡
ለኃጢአትና ለዲያብሎስ ባሪያ ሆኖ
መኖር ማብቃቱ የሰው ልጅ ያጣውን
ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት
ቀን ስለሆነ ነው፡፡ ራሱም ጌታችን
መድኃታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው
ልጅ ነጻነት ሲናገር ከእንግዲህ ወዲህ
ባሮች አልላችሁም፤ ባሪያ ጌታው
የሚደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆቼ
ግን ብያችኋለሁ በማለቱ /
ዮሐ.15፤15/ ከባርነት ነጻ የወጣንበት
ቀን መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ
ያስረዳል፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ
ክርስቲያን ከኃጢአት ባርነት በመራቅ
ከእግዚአብሔር ጋር የሚያወዳጀውን
መልካም ሥራ በመሥራት ሕይወቱን
በቅድስና መምራት ይኖርበታል፡፡ እርሱ
ጠላቶቹ ስንሆን ወዳጆቹ አድርጎናል፡፡ /
ማቴ 26፤17-19/
6.አረንጓዴው ሐሙስ ይባላል፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
በአትክልት ቦታ ስለ ጸለየ፡፡"ኪርያላይሶን
አቤቱ ይቅር በለን "

No comments:

Post a Comment