ቀዳም ሥዑር (የተሻረች ቅዳሜ)
የተወደዳችሁ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቤተሰቦች በሕማማት ሳምንት ውስጥ
ጌታችንና መድኃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰኞ እስከ ዓርብ ድረስ ያከናወናቸው
የድኅነት ሥራዎች እና በሣምንቱ የሚገኙ ዕለታት በቅድስት ቤተክርስቲያናችን የተሰጣቸውን
ስያሜዎች አይተናል፡፡ እነሆ ዛሬም ቅዳሜ ቀዳም ሽዑር ወይም የተሻረች ቅዳሜ፤ ለምለም
ቅዳሜ እና ቅዱስ ቅዳሜ ተብላ ለምን እንደተሰየመች እናያለን፡፡
ቀዳም ቀዳም ስዑር፣ ቅዳሜ ቀዳም ሥዑር መባሉ ከወትሮው ዕለታት በተለየ ይህችኛዋ
ዕለት የጌታችንን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምትውል የተሻረችው ቅዳሜ ትባለች፡፡
የማትፆመዋ ቅዳሜ ስለምትፆም ስዑር (የተሻረች) ተብላለች፡፡ በቀዳም ስዑር ሌሊት
ሥርዓቱ የሚጀምረው በማኅልየ ሠለሞን ምንባብ ነው፡፡ ማኅሌቱም እዝሉ እየተቃኘ
እየተመጠነ እየተዘመመ እየተመረደ እየተፃፈ ያድራል፡፡ ጥዋት አቡን መዋሥዕት ውዳሴ
ማርያም ዜማ ተደርሶ ወለመልአከ ሕይወትስ ሰቀልዎ በሚለው ሠላም ይጠናቀቃል፡፡
ለምለም ቅዳሜ መባሏም በዚህ ዕለት ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና ዲያቆናት ቄጤማ
ተሸክመው ቃጭል እያቃጨሉ የምሥራች አብሳሪ የሆነውን ቄጤማ ይዘው ወደ ምእመናን
ቤት ስለሚሔዱ ለምለም ቅዳሜ ትባላለች፡፡ ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና ዲያቆናት
ቄጤማ ተሸክመው ቃጭል ሲያቃጨሉ መታየታቸው ዕለተ ትንሣኤውን ለሚናፍቁ ምእመናን
ትልቅ ብስራት ነው፡፡
በቀዳም ስዑር ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ቃጭል እየመቱ ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሣኤሁ
አግሃደ የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ በመዘመር፤ ጌታ በመስቀሉ ሰላምን እንደሰጠን እና
ትንሣኤውንም እንደገለጠልን በማብሰር፤ ቄጤማውን ለምእመናን ይሰጣሉ፡፡ በዚህም
ምእመናን እስከ ትንሣኤ ሌሊት ድረስ ቀጤማውን በራሳቸው ላይ ያስሩታል፡፡ ይህም አይሁድ
ጌታችንን እያሰቃዩ ሊሰቅሉት ባሉ ጊዜ የእሾህ አክሊል ጭንቅላቱ ላይ ያሠሩበትን ድርጊት
የሚያስታውስ ነው፡፡
የቀጤማው አመጣጥና ምስጢርም ከአባታችን ከኖኅ ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ምድር በማየ
አይኅ /በጥፋት ውኃ/ በጠፋችበት ወቅት የኖኅ ታማኝ መልእክተኛ ርግብ የውኃውን መጉደል
ያበሰረችው ቀጤማ ይዛ በመግባት ነው፡፡ ዛሬም ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች የኃጢአት ውኃ
ጐደለ፣ የኃጢአት ውኃ ጠፋ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነጻነት ተሰበከ ታወጀ በማለት ካህናት
ቄጠማ ይዘው ምእመናንን ያበሥሩበታል፡፡
ቅዳሜ ቅዱስ ቅዳሜ ይባላል፡፡ ይህም ቅዱስ እግዚአብሔር አምላካችን በጥንተ ተፈጥሮ
ሃያ ሁለቱን ስነ ፍጥረታት የሚታዩትንና የማይታዩትን፣ በእግር የሚሄዱትን እና በክንፍ
የሚበሩትን፣ በባሕር የሚዋኙትንና በመጨረሻም ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረው
በዕለተ ዐርብ ሲሆን የመጀመሪያው ቅዳሜ ለእግዚአብሔር የዕረፍት ዕለት ናት፤
እግዚአብሔር ሥነ ፍጥረትን ፈጥሮ ስላረፈባት ሰንበት ዐባይ (ታላቋ ሰንበት) ትባላለች (ዘፍ.
1፡3) ይህችን ታላቋን ሰንበትም እንዲያከብሯት ሕዝበ እግዚአብሔር የተባሉ እስራኤላውያን
ታዘው ነበር፡፡
በዘመነ ሐዲስ ደግሞ የተለያየ የማዳን የድኅነት ሥራ ተከናውኖባታል፡፡ ጥንት ሥነ ፍጥረትን
በመፍጠር ዕረፍት እንደተደረገባት ሁሉ በሐዲስ ኪዳንም አዳምን ለማዳን ሕማምና ሞት
የተቀበለው ቸሩ አምላክ በሐዲስ መቃብር አርፎባታል (ማቴ. 27፡61)፡፡ በዚህም ጌታችን
መድኃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥራውን ሁሉ ፈጽሞ በሥጋው በከርሰ መቃብር
ሲያርፍ፣ በነፍሱ ሲዖልን በርብሮ ተግዘው የነበሩትን ነፍሳት ያወጣበትና ባዶዋን አስቀርቷታል፡፡
በዚያ ለነበሩት ነፍሳትም የዘለዓለም ዕረፍትን ያወረሰበት ዕለት ስለሆነ ከሌሎቹ ዕለታት
የተለየ ዕለት ለማለት ቅዱስ ቅዳሜ ተብላ ተሰይማለች፡፡
በዚህች ዕለት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከርሰ መቃብር ዐርፎ የዋለባት
ዕለት በመሆኗ በምሥጢር ከሰንበት ዐባይ ጋር ስለምትናኝ ቀዳሚት ሰንበት ተብላ
ትጠራለች፡፡ ቀዳም ስዑር (የተሻረች ቅዳሜ) የተሰኘችውም በዓመት አንድ ቀን ስለምትጾም
ነው፡፡ እናቱ ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም፣ ወዳጆቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታ ተላልፎ
ከተሰጠበት ዕለት አንስተው ብርሃነ ትንሣኤውን እስከሚያዩ ድረስ እህል ውኃ በአፋቸው
አልዞረም፡፡ ይመኩበትና ተስፋ ያደርጉት የነበረ መምህራቸው በመቃብር ስላረፈ ዕለቷን ነገረ
ሞቱን በማሰብና ትንሣኤውን በመናፈቅ በጾም አክብረዋታል፡፡
ከቅዱሳን ሐዋርያት ሲወርድ ሲወራረድ በመጣው ትውፊት መሠረት ቅዱሳን ሐዋርያት
በሐዘን፣ በጾምና በጸሎት ዕለቷን እንዳከበሯት ክርስቲኖችም የተቻላቸው ከዓርብ ጀምረው
በማክፈል፣ አሊያም ዓርብ ማታ በልተው ቅዳሜን በመጾም የጌታን ትንሣኤን ያከብራሉ፡፡
ቅዳሜ ጧት ምእመናኑና ካህናቱ ወደ ቤተ ክርስቲን ይሰበሰባሉ፡፡ የጧቱ ጸሎት ሲፈጸም
”ገብረ ሰላመ በመስቀሉ” በመስቀሉ ሰላምን መሠረተ፣ ሰላምን ፈጠረ፤ የምሥራች እየተባለ
በቤተ ክርስቲያን ለተሰበሰበው ሁሉ ቄጠማ ይሰጣል፡፡ የምሥራች ምልክት ነው፡፡
ምእመናኑም እየሰነጠቁ በራሳቸው ያስሩታል፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን ላልመጡት ምእመናንም
ካህናት በየሰበካቸው ልብሰ ተክህኖ ለብሰው መስቀልና ቃጭል ይዘው ቄጠማውን
የምሥራች እያሉ ያድላሉ፡፡
የዚህ የቄጠማው ታሪክ መነሻው የኖኅ ዘመን ታሪክ ነው፡፡ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን
በጻድቁ ኖኅ ዘመን የነበሩ ሰዎች በማየ አይህ ከጠፉ በኋላ የውኃውን መጉደል
እንድትመለከት የተላከች ርግብ የምሥራች ምልክት የሆነ ለምለም ቄጠማ በአፏ ይዛ
ተመልሳለች፡፡ በዚህም የውኃው መጉደል፣ የቅጣቱ ዘመን ማለፍ ተረጋግጧል (ዘፍ. 9፡
1-29)፡፡
ቄጠማ ለጥፋት ውኃ መድረቅ የምሥራች መንገሪያ እንደሆነው ሁሉ አሁንም በክርስቶስ ሞት
መተ ነፍስ ከሰው ልጆች ተወገደ ስትል ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ ቄጠማ ታድላለች፡፡
ምእመናንም የምሥራች ተምሳሌት የሆነውን ቄጠማ በግንባራቸው ያስሩታል፣ በጣታቸው
ቀለበት ያደርጉታል፡፡
የክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃን፣ ከሚያቃጥለው ዋዕየ ሲዖል
(የሲዖል ቃጠሎ) ወደ ልምላሜ ገነት፣ ጥንተ ማኅደራቸው መመለሳቸውን በዚህ አኳኋን
እየገለጡ ምእመናን በዓለ ትንሣኤን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያከብራሉ፡፡
ይህ የቅድስት ቤተክርስቲያናችን መሠረት ጌታችን መድኃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ
ክርስቶስ እንደሆነ ሁሉ ሥርዓቱም ይህ የተከተለ ነው፡፡ አንዳችም ቢሆን ከዚህ ውጭ የተሄደ
ነገር የለም፡፡ ስለዚህ ሥርዓተ ሕማሙን፤ ሰሙነ ሕማማት ብለው የተለየ ሥርዓት አውጥተው
አባቶቻችን ተግተው ያቆዩልንን ሥርዓተ መላእክት ልንጠብቀው እና ልንጠቀምበት ይገባናል፡፡
ቅደስት ቤተክርስቲያናችን አልተሳሳተችም ቤተሰቦችዋም አልተሳሳቱም መሠረታችን እሱ
የጌቶች ጌታ የአማልክት አምላክ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
ተኩላዎች የተባሉ ሃሳውያን መምህራን መናፍቃን ግን በተለያየ አሳቻ ዘዴ በመጠቀም
ከቅድስት ቤተክርስቲያናችን ሊነጥቁን ከቅድስት ቤተክርስቲያናችን ሊለዩን ዘወትር በበራችን፣
በምንመላለስበት መንገድ፣ በምንሠራበት ቦታ ይባስ ብለውም እውነተኛ መምህራን
መሥለው በመግባት በፀሎት ቤታችንም ጭምር አየገቡ ሊያታልሉን ሊለዩን ይሻሉ፡፡ እኛ ግን
መሠረታችን የሆነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሃሰተኛ መምህራንና መናፍቃን
ተጠንቀቁ ያለንን ቃል ምንጊዜም አንረሳም ሁሌም ከቅድስት ቤተክርስቲያናችን ዕቅፍ
ከእናታችን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም፣ ከቅዱሳን ሰማዕታት ፃድቃን በረከትና
ምልጃቸው ማንም አይለየንም ልንላቸው ይገባል፡፡ የዕለታቱን ክብርና ስያሜ ከማወቅና
ከመረዳት ጋር በዕለታቱ የታዘዙትን ሃየማኖታዊ ግዴታዎችን መወጣት ከሁላችንም
ይጠበቃል፡፡
እንበለ ደዌ ወሕማም እንበለ ፃማ ወድካም አመ ከመ ዮም ያብጽሐኒ ያብጽሕክሙ በፍስሐ
ወበሰላም፡፡

No comments:
Post a Comment